የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ለዎራት በመጠጥ ውኃ አቅርቦት እጦት


የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ለወራት በመጠጥ ውኃ አቅርቦት እጦት እና በቆሻሻ ሙሊት መጥፎ ጠረን እየተሰቃዩ መኾናቸውን በመግለጥ እያማረሩ ነው። የሐረሪ ክልል ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በበኩላቸው የሐረር የመጠጥ ውኃ ችግር በከፊል መፍትኄ አግኝቷል ። በአለማያ አካባቢ ያለው ትናንትና መፍትኄ ማግኘቱን ኾኖም የኤረር አካባቢ ያለው ግን ገና እየተሠራበት እንደኾነም ገልጠዋል። አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የሐረር ከተማ ነዋሪ የኮሌጅ መምሕር፤ በከተማዪቱ «የውኃ እና የቆሻሻ ብቻ ሳይኾን፤ የመንግሥት ሠራተኞችም ችግር» መንሰራፋቱን ተናግረዋል። ውኃውን አቋረጠ የተባለው አካል ጠየቀ ስለተባለው ብር መምሕሩ ሲያብራሩ፣ «ዐሥር ሚሊዮን የተባለውን እስኪ ይክፈሉ፤ እስኪ እንግዲህ ይኼ ውኃ ይለቀቅ። በቆሻሻው እኮ ምስክር ነው አሁን እየታየ ያለው ነገር። የተፈጸመው ጥፋት ነው ግን ለስርዓቱ ያላቸውን ጥላቻ ነው እያመለከቱ ያሉት» ብለዋል። «ጥያቄው የገንዘብ አይመስለኝም» ያሉት አስተያየት ሰጪው፦ «ይኼ ቄሮ ይሉሀል እንጂ፤ በስመ ቄሮ ይኹን እንጂ፤ የአካባቢው ሽማግሌ፤ ወጣቱ ምኑ ሳይቀር ነው አንድ ላይ ያለበት። ለምን በግልጽ አይናገሩም በቃ፤ ኅብረተሰቡ ነው ያመጸው» ሲሉ አክለዋል። «ሰዎቹ ይኼን ጥያቄ በገንዘብ ብቻ ያቆማሉ ወይ ነው? አይደለም። በገንዘብማ ያቆማሉ ከተባለ 18 ሚሊዮን ብር እኮ በቆሻሻ ተከፍሏል። ለምንድን ነው ያልቆመው? ቆሻሻ ለምን ተደገመ?» ሲሉ መምሕሩ በማብራራት መሠረታዊ ችግሩ «የስርአት ነው» ብለዋል። የሐረሪ ከተማ የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወለዳ አብዶሽ፦ «ከሁለቱ ችግሮች መካከል አንደኛው ትናንትና መፍትኄ አግኝቷል» ብለዋል። «ችግሩ ምንድን ነው? የሕግ የበላይነት አለመከበር ነበር። የውኃ አቅርቦትን የመቆራረጥ፤ ወይንም ደግሞ ወደ ከተማው እንዳይሄድ የመከልከል አዝማሚያ ነበር» ሲሉም ተናግረዋል። በአለማያ አካባቢ ያለው ትናንትና የምሥራቅ ኦሮሚያ የአወዳዩ እና የዓለማያ መስተዳደር ባደረጉት ጥረት የመደበኛ ሥራው እንዲቀጥል መደረጉን ጠቅሰዋል። «ይኼንንም ያሰናከሉ ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ የሚኾኑበትን መንገድም እያመቻቹ» መሆኑን ገልጠው፣ «በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችም እንዳሉ እና የኤረር አካባቢ ያለው ግን እስካሁን እየተሠራ ነው ያለው» ብለዋል።

Leave a comment