የለውጥ እርምጃዎች


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ከሰሞኑ እየወሰዳቸው ካሉ እርምጃዎች ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ያለው የጸጥታ ቁጥጥር ጥብቅ እንዲሆን መደረጉን ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ መጠናቀቁን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ላስተናገደው የአዲስ አበባ ነዋሪ እና ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል። በየደረጃው ያሉ የጸጥታ አካላት እና ፖሊስ በጋራ በመሆን እንግዶችን የማስተናገድ ኃላፊነትን “አኩሪ በሆነ ትጋት እና መናበብ” በበብቃት መወጣታቸውንም አውስተዋል። የህብረቱ ልዩ ጉባኤ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የሙስና ወንጀሎችን ፈጽመዋል በሚል በጠረጠራቸው ግለሰቦች ላይ እርምጃ እየወሰደ ባለበት ወቅት መከናወኑ የጸጥታ ቁጥጥሩን እንዳጠበቀው በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
“ሰሞኑን እየወሰድናቸው ካሉ እርምጃዎች ጋር በተያያዘ የጸጥታ ጥበቃው ጠበቅ ሊል እንደሚችል ኅብረተሰቡ ይገነዘባል ተብሎ ይታመናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ህዝብ ለለውጥ ሌት ተቀን እንደሚደክመው ሁሉ፣ ለውጡን ለማደናቀፍም ሌት ተቀን የሚደክሙ እኩያን የመኖራቸው ነገር ከማናችንም የተሰወረ አይደለም” ሲሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥ አደናቃፊ ያሏቸውን ኃይሎች በመግለጫቸው በግልጽ ባያመለከቱም “ዕንቅፋት ፈጥረው የሀገራችንን ገጽታ እንዲያበላሹ በምንም መልኩ ዕድል ፈንታ አንሰጣቸውም” ብለዋል።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የታደሙበትን የአፍሪካ ህብረትን ልዩ ጉባኤ ስታስተናግድ በቆየችው አዲስ አበባ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ስብሰባዎች ከታየው የበለጠ ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር መታየቱን ታዛቢዎች ተናግረዋል። ቀድሞ የስብሰባ ተሳታፊዎች በሚመላለሱባቸው ጎዳናዎች፣ በመሰብሰቢያቸው እና ማረፊያቸው አካባቢ የነበረው የጸጥታ ቁጥጥር ዘንድሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ መንደሮች ጭምር መስተዋሉን ታዛቢዎች ተናግረዋል።

Leave a comment